በእውቀት የሚመራ ፕላን ለነገዋ አዲስ አበባ"፤...

image description
- ውስጥ ዜና    0

በእውቀት የሚመራ ፕላን ለነገዋ አዲስ አበባ"፤ የ10ኛው መዋቅራዊ ፕላን የፋይዳ ግምገማ የመነሻ ፅንሰሃሳብ ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ | ሚያዚያ 2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ልማት ቢሮ "በእውቀት የሚመራ ፕላን፣ በቅንጅት የሚለማ ከተማ!" በሚል መሪ ቃል፣ የከተማዋን የ10ኛው መዋቅራዊ ፕላን ውጤታማነት እና የፋይዳ ግምገማ በሚመለከት በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውን የመነሻ ፅንሰሃሳብ ሪፖርት (Inception Report) ለባለድርሻ አካላት አቅርቦ አስገመገመ።

በቢሮው መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው በዚህ የምክክር ወርክሾፕ ላይ፣ "የታቀደ ልማት ለተሟላ የከተማ ብልጽግና!" በሚል እሳቤ የጥናቱ መነሻ ሰነድ በቀረበበት ወቅት፤ ጥናቱ በዘጠኝ (9) ዋና ዋና ከተማ ነክ ጭብጥ ጉዳዮች (Thematic Issues) ላይ ትኩረት ማድረጉ ተገልጿል።

የጥናቱን ሰነድ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ሳምሶን ካሳሁን፤ በ10ኛው መዋቅራዊ ፕላን ውጤታማነት ላይ በዘጠኙም ጭብጥ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ግምገማው የሚከናወንባቸውን ሳይንሳዊ ስልቶችና የጥናት አካሄዶች ለተሳታፊዎች በዝርዝር አስረድተዋል።

የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ውጤታማና ጥራት ያለው የፕላን አፈጻጸም ለነገዋ አዲስ አበባ ወሳኝ ነው" ካሉ በኋላ፣ የፋይዳ ግምገማው በተለይም በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ማለትም፦ በመሬት አጠቃቀም ጥምርታ (Land Use Mix)፣ በህንፃ ከፍታ፣ በመንገድና መጓጓዣ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ኃላፊው አክለውም ባለድርሻ አካላት በጥናቱ ሂደት ላይ በንቃት በመሳተፍ ግብዓት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ምትኩ አዲሱ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ግዙፍና ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ጥናት በጨረታ አሸንፎ መስራቱ ካለበት የማህበራዊ ኃላፊነት አንጻር የሚያኮራ መሆኑን ገልጸው፤ የተጣለባቸውን አደራ በብቃትና በጥራት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ፤ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደር ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ የቡድን መሪዎች፣ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ተገኝተው በሰነዱ ላይ ጥልቅ ውይይት አድርገዋል።

ይህ የፋይዳ ግምገማ ጥናት መጠናቀቅ የከተማዋን ቀጣይ የልማት አቅጣጫዎች በውጤታማነት ለመምራት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ይጠበቃል።

***
ሚያዚያ 2018 ዓ.ም


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.