
የወርቃማ ሰኞ የዕውቀት ሽግግር እና ተሞክሮ ልውውጥ ያመጣው ውጤት ተገመገመ፡፡ (ፕላንና ልማት ቢሮ፣ ሰኔ 30/2017 ዓ.ም)
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት በየሳምንቱ ሰኞ ማለዳ ‘የወርቃማ ሰኞ’ በሚል አውድ በአመራሮችና እና ሠራተኞች ሲካሄድ የቆየዉ የወርቃማ ሰኞ የዕውቀት ሽግግር እና ተሞክሮ ልውውጥ ያመጣው ውጤት ተገመገመ፡፡
በቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ንጉሴ እንደገለፁት የግምገማ ዓላማው በየሳምንቱ የሚደረጉ የወርቃማ ሰኞ ፕሮግራም የተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች ያካበቱት የተለያዩ የስራ ልምድ ተሞክሮች፣ ያሳለፉት የህይወት ውጣ ውረዶች፣ በሀገር እና ከሀገር ውጭ ያገኙትን ተሞክሮዎች፣ የተፈጠረውን የስራ መስተጋብር እንዲሁም ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን በመገምገም በቀጣይ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል ነው ብለዋል፡፡
በዕለቱ የተቋሙን ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴቶች በዝርዝር ያብራሩት አቶ ተስፋዬ በወርቃማው ሰኞ ስለተቋሙ አገልግሎቶች፣ ለስራ አጋዥ የሆኑ እውቀቶች እና የህይወት ልምዶች የተጋሩበትና የተላለፉበት መድረክ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በቢሮዉ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ ዝግጅት ባለሙያ አቶ ታሬሳ ጃለታ እንደገለፁት የወርቃማ ሰኞ ፕሮግራም ከብዙ የስራ ባልደረቦች ጋር እንድንተዋወቅ እና አዳዲስ ነገሮችን እንድንናወቅ አድርጓል በዚህም ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
በቢሮዉ የኢኮኖሚ ልማት ፕላን ተወካይ ቡድን መሪ ወ/ሮ ንግስቲ መንግስቱ እንደገለፁት በፕሮግራሙ ላይ የሚቀርቡ ተምክሮች አስተማሪ ናቸው እርስ በርስ እንድንማማር አደርጎናል በማለት ተናግረዋል፡፡
በቢሮው የጂአይኤስ ባለሙያ አቶ ኢሳያስ ተሾመ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ጥሩ የስራ ስሜት የፈጠረ እና ፕሮግራሙን በናፍቆት እንድንጠበቅ አድርጓል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የወርቃማ ሰኞ ፕሮግራም ያመጣውን ለውጥ፣ የነበሩ ጥንካሬዎች እና ድክመቶችን በመገምገም በቀጣይ የሚሻሻሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.