ስምምነት ረቂቅ ሰነድ

አንድ ሀገር /ከተማ ለዘጎች የሚሰጠውን አገልግሎት በጥራትና በስታንዳርድ ለማቅረብ ዓለም አቀፋዊ ልምዶችንና አሠራሮችን በሳይንሳዊ ጥናትና ቴክኖሎጂ ማስደገፍ አስፈላጊ ነው።
በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ልማት ኮሚሽን የሚሰጣቸው አገልግሎች የረዥም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ገፀ-ምድራዊ /Spatial/ ፕላኖች የማዘጋጀት፣ አፈፃፀማቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር፤ እንዲሁም ሴክተር መ/ቤቶች ከስልታዊ ዕቅድ ጋር ተናባቢ ዕቅድ ማዘጋጀታቸውን የመከታተል፣ የማረጋገጥ፣ አፈፃፀማቸውን የመቆጣጠር፣ የመመዘንና ደረጃ የማውጣት ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን በልማት ፕላን ዝግጅትና አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን የመለየት፣ ጥናትና ምርምር ስራዎችን የመስራት፣ ለከተማው ተግዳሮት ተቋቋሚነት (Resilience) የሚያግዙ ተግባራትን የመፈፀም፤ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለውሳኔ ሰጪነት በግብዓትነት የሚያገለግሉ መረጃዎችን ከተቋማት በማሰባሰብ የማደረጀት፤ የማቀናበር፣ የመሰነድ፤ የማሰራጨትና የማስተዳደር እንዲሁም በፕላን ዝግጅት ወቅት የሕዝብ ተግባቦትና ስርፀት እንዲሁም መሰል ሥራዎችን ለማከናወን እንዲችል በአዋጅ ቁጥር 74/2014ዓ.ም. መሠረት ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል፡፡
ኮሚሽኑ ለነዋሪዎች ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያደረገ ቢሆንም በከተማው ፈጣን እድገትና እያደገ የመጣውን የዜጎች የአገልግሎት ፍላጎት ለማርካት ክፍተቶች የታዩ በመሆናቸው የተገልጋዩን ፍላጎትና የከተማዋን የእድገት ጉዞ ለማሳለጥ በሚያስችል ሁኔታ የኮሚሽኑ የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ማሻሻያ /Bussiness Process Improvement/BPI/ ተጠንቶ ጸድቋል።
በዚህ መሠረት ኮሚሽኑ የሚሰጠው አገልግሎት የተገልጋይ ፍላጎትን ማዕከል አድርጎ ይበልጥ ተደራሽ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ለማስቻል የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ የሚሰጥበት ስታንዳርድ፣ አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ቦታ እና ከተገልጋይ የሚጠበቁ ቅድመ ሁኔታዎችን በግልጽና በዝርዝር በማስቀመጥ የኮሚሽኑ አመራሮችና ሠራተኞች ሊተገብሩትና ሊከተሉት የሚገባ የዜጎች ስምምነት ቻርተር ተዘጋጅቷል፡፡